የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት በጥራት መሰረተ ልማት፣ በልኬት መሰረታዊ ሀሳብ፣ በስነ-ልክና በህጋዊ ስነ-ልክ ምንነት ዙሪያ ለሲዳማና ለደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የንግድ ቢሮ ኃላፊዎችና ለህጋዊ ስነ-ልክ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

.የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት በጥራት መሰረተ ልማት፣ በልኬት መሰረታዊ ሀሳብ፣ በስነ-ልክና በህጋዊ ስነ-ልክ ምንነት ዙሪያ ለሲዳማና ለደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት የንግድ ቢሮ ኃላፊዎችና ለህጋዊ ስነ-ልክ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በፕሮጋረሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን ፣የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቢሮ ኃላፊና የንግድ አሰራር ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባጥሶ ዌድሶ እንዲሁም የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ዳይሬክተርና ተወካይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸርነት ፈቃዱ በተከታታይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን እንደገለፁት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በልኬት ሳይንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን በተለይ አምራቹና አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪው የሚያመርቷቸው ምርቶች ጥራት እንዲኖራቸው ብሎም ወጥነትና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የአለካክ ሥርዓት በመዘርጋት ፍትሀዊ የንግድ ስርዓት እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ይህን ስራ ማሳካት የሚቻለው እንደዚህ አይነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ቴክኒካዊ ብቃትና በስነ-ምግባር የታነፀ ባለሙያ ማፍራት ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም መድረኩ የተሳካ እንዲሆን ሁለቱ ክልሎች ላደረጉት ትብብር ምስጋና ያቀረቡት ዳይሬክተሩ በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ በኩል የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድና ኢንዱስትሪ ም/ቢሮ ኃላፊና የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባጥሶ ዌዲሳ እና የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ዳይሬክተርና ተወካይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቸርነት ፈቃዱ እንደተናገሩት የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ በናረበትና ብዙ የልኬት ማጭበርበር ወንጀሎች በሚፈፀሙበት በዚህ ወቅት ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘጋጀቱ ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑን አውስተዋል፡፡ አንዳንድ የንግድ ተቋማት የልኬት መሳሪያዎችን በመቀሸብና ክብደትን በማሳነስ ህብረተሰቡን እያማረሩ እንደሚገኙና መንግስት የሚመራውን ህዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ ስላለበት በእነዚህ ህገወጦች ላይ እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አብዱራህማን የተቋሙን አመሰራረትና አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በሌላ በኩል በኢንስቲትዩቱ የዋና ዳይሬክተር አማካሪና የኤሌክትሪካል ጊዜና ድግግሞሽ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ነስረዲን ነዚር እንዲሁም ከፍተኛ የሜካኒካል ካሊብሬሽን ባለሙያ አቶ ሰለሞን አሰፋ የግንዛቤ ማስጨበጫውን ሰጥተዋል፡፡ ርዕሰ ጉዳዮችም ስነ-ልክና በጥራት ላይ የሚጫወተው ሚና፣ ስለህጋዊ ስነ-ልክ ምንነት፣ ፋይዳዎች፣ የስነ-ልክ ሕግ አወጣጥ መሰረታዊያን፣ የተለመዱ የቁጥጥር ተግባራት ፣ ለህጋዊ ስነ-ልክ ኦፊሰሮችና በኦፊሰሮች ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሳሪያዎች፣ የነዳጅ መቅጃ ዲስፔንሰር ቬሪፊኬሽን፣ የሚዛኖች ቬሪፊኬሽን እና የክብደት ማነፃፀሪያዎች ቬሪፊኬሽን የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች መሆናቸውን መረዳት ተችሏል፡፡ በመጨረሻም በከተማው በሚገኝ አንድ የነዳጅ ማደያ ላይ የተግባር ልልምድ የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ከመድረክ ምለሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
Comments(0)