አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2016 ዓ.ም (ኢስኢ) የተለያዩ ውጣውረዶችን ሲያልፍ የቆየው የኢትዮጵያ ቤተ-ሙከራዎች ማህበር (ELA) የዳግም ምስረታ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ የማህበሩ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት የሳይንሳዊ ሥነ-ልክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሠ ጌርጊሶ እና በኢትዮጵያ የጀርመኑ ሥነ-ልክ ተቋም(ፒቲቢ) ፕሮጅክት አስተባባሪ ሚስተር ኡኩሜ ኢኮን አርቺቦን የእንኳን ደህና መጣችሁና የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቤተሙከራዎች ማህበርን ተሞክሮ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደርበው እንዳሉት ለፍተሻ፣ ለኢንስፔክሽን፣ ለቬሪፊኬሽን፣ ለምርምር እና ስርፀት፣ ለኢንዱስትሪዎች ቁጥጥር ላቦራቶሪዎች እንዲሁም ለአናሊሲስና ለመለኪያ መሳሪያዎች ወይም ለልኬትና እርከን ተዋረድ ትስስር እና ለጥገና አገልግሎቶች ብቃትና ተደራሽነት ማደግ ሁነኛ ሚና የሚኖረው የኢትዮጵያ ቤተ-ሙከራዎች ማህበር (ELA) መልሶ ማቋቋሚያ ጠቅላላ ጉባኤ በመካሄዱ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሙሉጌታ አክለው እንዳሉት የኢትዮጵያ ቤተ-ሙከራዎች ማሕበር ከተመሰረተ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ባለፈባቸው ውጣውረዶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት ለረጅም ጊዜ ፕሬዚደንት ሆኖ ከመምራቱ በተጨማሪ ማሕበሩ ለሀገር ሊሰጥ የሚችለውን ወሳኝ ጠቀሜታ በቅጡ በመገንዘብ ከአጠቃላይ መዳከምና ብሎም መጥፋት ለመታደግ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የራሱን የማይጠፋ አሻራ ማኖሩን ገልፀዋል፡፡ ጠንካራ የጥራት መሰረተ ልማት በመገንባቱ ሂደት የማህበሩን ሚና በሚገባ በመረዳት ሚኒስትር መስሪያ ቤቶቻችን ላደረጉልን ድጋፍና ክትትልም ማመስገን ይገባል ሲሉ አስምረውበታል። መላው የማህበሩ መስራች አባላትም የሀገርን ገጽታ፣ የምርትና አገልግሎት ተዓማኒነት ሊገነባ ለሚችለው ማህበር ጠንክሮ መውጣት እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ ቤተሙከራዎች ማህበር ህጋዊ ሰውነቱን በማግኘት ሂደት ባገጠሙት ተግዳሮቶች ተስፋ ባለመቁረጥ የጀርመን ሥነ-ልክ ተቋም (PTB) ከቀደመው የማህበሩ ምስረታ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በገንዘብና በቴክኒክ ረገድ ያደረገው ድጋፍ እውቅና የሚገባውና የሚመሰገን መሆኑን ጠቁመዋል። ማህበሩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት እና PTBን ከማመስገናቸው በተጨማሪ የኢትዮጵ ደረጃዎች ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ አክሬድቴሽን አገልግሎትም ተጋብዘው ለማህበሩ መጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማስቻል እንደሚገባም ጠቁመዋል። የጥራት መሰረተ ልማት ተቋማት ተጠሪ የሆኑባቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማህበሩን በልዩ ሁኔታ የሚደግፍበት አግባብም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት ያስፈልጋል።
.
Comments(0)